የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚገኙ ዜጎቹ በኢትዮጵያ ላሉና ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ ላቀዱ ዜጎቹ የጉዞ ማስጠንቀቂያ አወጣ

የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ዜጎች ከኢትዮጵያ ለመውጣት ዝግጅት እንዲያደርጉ እንዲሁም ወደ ኢትዮጵያ የሚደረግ ጉዞ ያላቸው ዕቅዳቸውን በአንክሮ እንዲያጤኑት አሳስቧል።

ይህ የኤምባሲው ዜና የተሰማው የኢትዮጵያ መንግሥት በመላው አገሪቱ ለስድስት ወራት ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 23/2014 ዓ.ም መደንገጉን ካሳወቀ በኋላ ነው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያስተላለፈው አዋጅ ዋነኛ ዓላማ የአገሪቱ ዜጎች “በሽብር ቡድኑ የሚደርስባቸውን ጥቃት መመከት” መሆኑ የተገለጸ ሲሆን አዋጁም ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።

ኤምባሲው ለዜጎቹ ባስላለፈው መልዕክት “የአሜሪካ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ የመጓዝ ውሳኔያቸውን በአንክሮ እንዲያስቡበት እና በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ዜጎች ደግሞ ከአገር ለመውጣት ዝግጅት እንዲያደርጉ አጥብቀን እንመክራለን” ይላል።

በአሁኑ ወቅት የኤምባሲው ሠራተኞች ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ መጓዠ እንደማይፈቀድላቸው አስታውሶ፤ ባለፉት በርካታ ቀናት በአማራ፣ በአፋር እና በትግራይ ክልሎች ተባብሶ የቀጠለው ግጭት እና አመጽ በኢትዮጵያ ያለውን የደኅንነት ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ አስጊ አድርጎታል ብሏል።

አንድ ዓመት ሞላው በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እተባባሰ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋ ሲሆን የፌደራል መንግሥቱና የክልል አስተዳደሮች የአማጺያኑን እንቅስቃሴ ለመመከት ለሕዝቡ ጥሪ አቅርበዋል።

 

Spread the love


Comments are Closed