Main Menu

በቤተ እምነቶች ላይ ጥቃት መፈጸም ማለት ለዘመናት የተገነቡ የጋራ እሴቶችን ማውደም ማለት ነው

በቤተ እምነቶች ላይ ጥቃት መፈጸም ማለት፣ ለዘመናት የተገነቡ የጋራ እሴቶችን ማውደም ማለት ነው

‹‹ካልደፈረሰ አይጠራም›› በሚል አጉል ብሒል የተለያዩ ግጭቶች እየተቀሰቀሱ፣ በሕዝብ ሕይወትና ንብረት ላይ የሚዘገንኑ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ ብሔርን ወይም ማንነትን ተገን ያደረጉ እርኩሳዊ ድርጊቶችን ወደ ሃይማኖት መውሰድ በጣም አደገኛ ነው፡፡ በቤተ እምነቶች ላይ ጥቃት መፈጸም ማለት፣ ለዘመናት የተገነቡ የጋራ እሴቶችን ማውደም ማለት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በታቦቶች ላይ ድንጋይ መወርወሩ ሲሰማ እንደ ዘበት ታልፎ፣ አሁን ደግሞ መስጊዶች መቃጠላቸው ተሰምቷል፡፡ እንዲህ ዓይነት መረን የለቀቀ ሕገወጥና ሥርዓተ አልበኝነት እንደ ተራ ወንጀል የሚታይ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያዊነት ላይ የተቃጣ አደገኛና ነውረኛ ድርጊት መሆኑን መተማመን ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር የድርጊቱን ፈጻሚዎች በማውገዝ፣ ተገቢው ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው በአንድነት ድምፁን ማሰማት አለበት፡፡ በየትኞቹም ቤተ እምነቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት የጋራ መሆኑን የሚገነዘበው አስተዋዩና ጨዋው ሕዝብ፣ እኩዮችን ከውስጡ አበጥሮ በማውጣት ሕግ ፊት የመገተር ግዴታ እንዳለበት ይረዳል፡፡ በተግባር እንደሚያሳይም ይጠበቃል፡፡ ይኼንን ማረጋገጥ ሲቻል የደፈረሰው ጠርቶ እውነታው ይታወቃል፡፡ ነውረኞችን መታገስ አያስፈልግም፡፡

ኢትዮጵያ ለአሥር ወራት የዘለቀ የለውጥ ማዕበል ውስጥ ናት፡፡ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ዓለምን ያስደመሙ በርካታ አዎንታዊ ተግባራት ሲከናወኑ፣ በተቃራኒው አንገት የሚያስደፋ አሉታዊ ድርጊቶችም በስፋት ተስተውለዋል፡፡ ለውጥ ውስጥ ባለች አገር መልካም ነገሮች ያሉትን ያህል ክፉ ድርጊቶችም መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ካለፉት ስህተቶች በመማር ትክክለኛውን ጎዳና መያዝ ሲቻል፣ ነጋ ጠባ ለአገር ህልውና ሥጋት የሚፈጥሩ ድርጊቶችን መፈጸም ወይም ተባባሪ መሆን ያሳዝናል፡፡ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የወደፊቱን ተስፋ ከማየት ይልቅ፣ እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ ሲሉ ከማየት የበለጠ አሳዛኝ ነገር የለም፡፡ የብሔር ግጭት በመቀስቀስ የንፁኃንን ሕይወት ማጥፋት አልበቃ ብሎ፣ እጅግ አደገኛ መዘዝ ሊያስከትል የሚችል የሃይማኖት ግጭት ለማስነሳት መሞከር የማይወጡበት አዘቅት ውስጥ ይከታል፡፡ ከዚህ በፊት ዓይን ለዓይን መተያየት ቀርቶ በሩቁም ቢሆን መቀራረብ የማይፈልጉ ፖለቲከኞች፣ አንድ አዳራሽ ውስጥ ተቀምጠው ሐሳብ መለዋወጥ በጀመሩበት በዚህ ተስፋ ሰጪ ጊዜ ያልተገባ ድርጊት ውስጥ መገኘት አያዋጣም፡፡ ሰላማዊውን ድባብ እያደፈረሱ ትርፍ ፍለጋ መባዘን ለኪሳራ ይዳርጋል፡፡ ይኼንን ኪሳራ በሕዝብ ላይ ለማወራረድ መሞከር ደግሞ አዘቅት ውስጥ ይከታል፡፡

የአገሪቱ የፖለቲካ ባህል ውርስ የሆኑት ጥላቻ፣ ቂም፣ ክፋት፣ ሴራና የመሳሰሉት እኩይ ድርጊቶች ያስገኙት ቢኖር መጠፋፋት ብቻ ነው፡፡ አንዱ ጉልበተኛ መንበረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ ይገዳደሩኛል የሚላቸውን መግደል፣ ማሰቃየት፣ ማሰርና ማሳደድ ዋነኛ ተግባራቱ እንደነበሩ ለዓመታት ታይቷል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ ኋላቀርና የኪሳራ ፖለቲካ ውስጥ በመውጣት ሜዳውን በጋራ በማመቻቸት ለመፎካከር እንዘጋጅ ሲባል፣ ከጠባብ ዕይታ ውስጥ ለመውጣት አቅምም ሆነ ዝግጅት የሌላቸው እየተሹለኮለኩ አገር ያምሳሉ፡፡ ግለሰቦችን አጣልተው የብሔር ገጽታ በማላበስ ንፁኃንን ያስፈጃሉ፣ ያፈናቅላሉ፣ የአገር ሀብት ያወድማሉ፡፡ ይህ አልበቃ ሲላቸው ደግሞ በቤተ እምነቶች ላይ ጥቃት በመፈጸም ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የሃይማኖት ፍጅት ለመፍጠር ይቅበዘበዛሉ፡፡ አስተዋዩና ጨዋው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ያደራጃቸውን የጋራ እሴቶቹን በመናድ የፖለቲካ ትርፍ ማግኘት አይቻልም፡፡ በዚህ እሳቤ ውስጥ ሆኖ ለተወሰኑ ጊዜ ችግር መፍጠር ቢቻልም፣ የደፈረሰው የጠራ ጊዜ ግን እኩዮች የእጃቸውን ያገኛሉ፡፡ ሕዝብ እነዚህን በከፍተኛ ጥንቃቄ መከታተል አለበት፡፡ በሕይወቱና በአገሩ ላይ እንዲቆምሩ መፍቀድ የለበትም፡፡

መሰንበቻውን የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ አዳራሽ ውስጥ ተገናኝተው መወያየታቸው በጣም የሚደገፍ ተግባር ነው፡፡ የሰላማዊ ፖለቲካ የጨዋታ ሕግ የሚፈልገው ጨዋነትንና ጥብቅ ዲሲፕሊንን ነው፡፡ የሐሳብ ገበያው በደራ መጠን የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕዝብ የህሊና ዳኝነት ፍርድ ይንገዋለላሉ፡፡ የተሻለና የደረጀ ሐሳብ የሰነቀው የሕዝብን ቀልብ ሲገዛ፣ የተበለጠው ደግሞ በተሻለ ሐሳብ ለመገኘት ራሱን ያዘጋጃል፡፡ ሐሳብ ያጠረው ከሌሎች በመማር ወይም ከተሻሉት ጋር በመዳበል ጠንክሮ ይቀርባል፡፡ ይኼንን ዴሞክራሲያዊ መንገድ መከተል የማይፈልግ ደግሞ ወደ ጥፋት ይሰማራል፡፡ አጥፊን ደግሞ ሕግ አደብ ያስገዛዋል፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የሠለጠኑ አገሮች የሚጠቀሙበት ሥልት ነው፡፡ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚፎካከሩበት መድረክ ሲሆን፣ ዕውቀትና ልምድ ያላቸው ከወጣቶች ጋር በመቀናጀት ድንቅ የፖለቲካ ክህሎት ያሳዩበታል፡፡ በዚህ መሠረት መንቀሳቀስ ሲቻል አገር ከረሃብ፣ ከድንቁርና ከኋላ ቀርነትና ከመሳሰሉት አስከፊ ውርሶች ነፃ የሚያወጣት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ትገነባለች፡፡ የደፈረሰው ጠርቶ ነፃነት፣ ፍትሕና እኩልነት ይረጋገጣሉ፡፡

ለኢትዮጵያዊያን አገር ማለት ታላቅ በረከት ናት፡፡ የማንነት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ የእምነትና የመሳሰሉት ልዩነቶች መኖራቸው እስከማያስታውቅ ድረስ የጋራ እሴቶች ጎልተው የሚወጡባት አገር ናት፡፡ ከልዩነቶች በላይ የጋራ የሆኑ ጉዳዮች በጣም ከመብዛታቸው የተነሳ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጋብቶና ተዋልዶ አብሮ የሚኖር ነው፡፡ ይህ ዘመናትን የተሻገረ የጋራ እሴቶች ባለቤትነት ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ታላቅ ተምሳሌትነት ያለውን ታላቁን የዓድዋ ድል ያጎናፀፈ ነው፡፡ መላው ሕዝባችን ከአራቱም ማዕዘናት ዘምቶ የአውሮፓን ኮሎኒያሊስት ኃይል የዓድዋ ተራሮች ላይ በማንበርከኩ ነው፣ ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም ጽንሰ ሐሳብ እንዲጀመር ያስቻለችው፡፡ በዚህ ታላቅ ድል ምክንያት ነው የኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እንድትሆን አፍሪካውያን የወሰኑት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከልዩነቶቹ በላይ የጋራ እሴቶቹ እጅግ የገዘፉ በመሆናቸው ነው፣ አገሩን ቅኝ ገዥዎች ሳይቀራመቷት በነፃነት ያቆያት፡፡ ይህ ታላቅ፣ ኩሩ፣ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ አገሩ ስትነካ አይወድም፡፡ ወገኑ ሲጠቃ ያመዋል፡፡ ለአፍሪካውያን ወንድሞቹና እህቶቹ ነፃነት የተዋደቀ ይህ ታላቅ ሕዝብ፣ እንኳንስ እርስ በርሱ ሊጣላ በመሀሉ ንፋስ እንዲገባ አይመኝም፡፡ ሕዝብን እርስ በርሱ ለማፋጀት በተለያዩ መንገዶች ጥላቻ የሚዘሩና ግጭት የሚቀሰቅሱ አደብ ይግዙ፡፡ እጃቸውን ይሰብስቡ፡፡ ሃይማኖትን አጀንዳ በማድረግ የጥፋት እጃቸውን የሚያስረዝሙም ልብ ይበሉ፡፡ አያዋጣም፡፡ አሁን ለጊዜው የተሳካላቸው የሚመስሉ እዚህም እዚያም ግጭት ቢፈጥሩ፣ በሕዝባችን የተከበረ ክንድ ይመክናሉ፡፡ የደፈረሰው መጥራቱ ስለማይቀርም በሕግ አደብ ይገዛሉ!

የጋራ እሴቶችን የሚንዱ ነውረኞች በሕግ አደብ ይግዙ!

ሪፓርተር

Spread the news


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked as *