Main Menu

‘የዜግነት ፖለቲካ’ የሚባል ነገር የለም! ካለም ከ’ማንነት ፖለቲካ’ ባልተሻለ ደረጃ አግላይ ነው!

‘የዜግነት ፖለቲካ’ የሚባል ነገር የለም! ካለም ከ’ማንነት ፖለቲካ’ ባልተሻለ ደረጃ አግላይ ነው–ለኤፍሬም ማዴቦ የተሰጠ አጭር ምላሽ

ሰሞኑን በLTV show ‘ሰፊው ምሕዳር’ ፕሮግራም (ክፍል 2) ላይ፣ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ከሌሎች ሁለት ተወያዮች ጋር ቀርቦ ሲከራከር፣ ስለ ማንነት ፖለቲካ አግላይነት፣ ስለ ዜግነት ፖለቲካ አቃፊነት በመግለፅ ሲከራከር ተመለትኩ። የአፄ ምኒልክን አገዛዝ አስመልክቶም፣ ንጉሡ አገር በመገንባት ሂደት ውስጥ፣ ልክ ሁሉም አገር ገንቢዎች እንደሚያደርጉት (ለምሳሌ ቢስማርክ በጀርመን፣ ጋሪባልዲ በጣልያን) እንዳደረጉት የኃይል ተግባር እንደተጠቀሙ፥ ይሄም የሳቸውን የተለየ እንደማያደርገው፥ ጊዜው ዴሞክራሲ ያልነበረበት በመሆኑ በወቅቱ ንጉሡም ዴሞክራት እንዳልነበሩ፥ ጥፋትና ፍጅት ቢፈፅሙም ትልቅ አገር እንደፈጠሩልንና እንዳወረሱን፥ ወዘተ እየጠቀሱም ተከራከረ። እዚህ፣ በሱ የክርክር ጭብጦች ላይ የሰጠሁትን አስተያየት እንደሚከተለው አቀርባለሁ።

1. ማንነት አግላይ ከሆነ (በተፈጥሮው አግላይ ነው ብዬ አላምንም)፣ ኢትዮጵያዊነት የሚባለው ማንነትስ አግላይ እንደሆነ መረዳት እንዴት ተሳናቸው፣ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ? ዜግነት ዋና ማግለያ አይደል እንዴ? ፓስፖርት (አለመያዝ) ዋናው ማግለያ መሣሪያ አይደለም እንዴ? “የዜግነት ፖለቲካ” (ያውም የሚባል ነገር ካለ!) እንዴት ነው አግላይ ያልሆነው?

2. በሚኒልክ ጊዜ፣ በዓለም ላይ ዴሞክራሲ አልነበረም? ውሸት!!! በአሜሪካ ከ1776 ጀምሮ (በተለይ ከ1865 ጀምሮ)፣ በእንግሊዝ ቢያንስ ከ1625 ጀምሮ፣ በፈረንሳይ ቢያንስ ከ1789 ጀምሮ፣ በሄይቲ (እንኳን) ከ1804 ጀምሮ በምርጫ የሚገለፅ፣ በአብዛኛው ሊበራል ብቻ የሆነ (ምናልባትም ከሄይቲ በቀር ሌሎቹ ጋ የቡርዧ) ዴሞክራሲ ነበረ። ዘመኑ የዴሞክራሲ አልነበረም ቢባል እንኳን፣ በዘመኑም ሕግና ልማድ መሠረት፣ የሚኒልክ መስፋፋት፣ ከአውሮፓውያን ወረራ የከፋ አረመኔያዊ ተግባር እንደነበረ፣ የራሱ የምኒልክ አውሮፓውያን አማካሪዎቹ(እንደ Bulatovitch ዓይነቶቹ) በዝርዝር ፅፈውታል።

3. እሺ፣ አውሮፓያውያኑ ልክ እንደምኒልክ ያጠፉ ነበር ብንል እንኳን፣ ለመሆኑ እነሱ ማጥፋታቸው ምኒልክን ትክክል ያደርገዋልን?

4. “German እና ጣልያን የተዋኅዱት በኅይል ነው፣ የኛም ከዛ አይለይም፣” የሚለው ክርክር አንደኛ፣ ተጨባጭ እውነታነት የለውም። ሁለተኛ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይነት የለውም። ሶስተኛ፣ እውነት ቢሆንምና ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳስይነት ቢኖረውም እንኳን፣ እነሱ ጋር የተፈፀመውና ኢትዮጵያ የተፈፀመው ጥፋት፣ በመጠንም በዓይነትም የሚወዳደር አይደለም። አራተኛ፣ ይሄም ሁሉ ቢሆን እንኳን፣ እዛ መፈፀሙ፣ እዚህ የተፈፀመውን ትክክል አያደርገውም።

ጀርመንን ቢስማርክ ያዋሃደው በተለያዩ የጀርመን ፕሪንሲፓሊቲስ የሚኖሩ የጀርመን ብሔር የሆኑ ሕዝቦችን ነው እንጂ የጀርመን ብሔር ያልሆኑ ሕዝቦችን ጀርመን በማድረግ አይደለም። ጣልያንን በኃይል ጋሪባልዲ ሲያዋህድ፣ እንዲሁ በተለያዩ Italian principalities ሥር ይኖሩ የነበሩትን የጣልያን ብሔር አባላትን ነው እንጂ ሌሎችን ጣልያን በማድረግ አልነበረም።

የጀርመንና የጣልያን የውህደት ታሪክ የአገር ግንባታ (nation-building) ታሪክ ነበር። ማለትም፣ አንድ ሕዝብ በአንድ አገርና በአንድ መንግሥት ሥር የሚተዳደርበት (nation-state የመፍጠርና) ሥርዓት የመመሥረት ዓላማ ነበረው። የምኒልክ መስፋፋት ግን የአገር ግንባታ (nation-building) ተግባር ሳይሆን የተስፋፊ ነገሥታት ጠቅላይ ግዛት መፍጠር (empire building) ተግባር ነበር። አቢሲንያን nation-state building (ሸዋን፣ ከጎጃም፣ከጎንደር፣ ከትግሬ፣ ወዘተ ጋር በአንድ ንጉሠነገሥት ሥር በሚያሰባስቡበት ሂደት ተፈፅሟል። የቴዎድሮስ በ1855 ማሸነፍና መንገስ፣ የአቢሲኒያን nation-state ግንባታ ሂደት ወደ ማገባደጃው መድረሱን ያሳይ ነበር። ከ1880ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የሆነው ነገር፣ አቢሲኒያ ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦችን በወረራ በአቢሲኒያ ሥር የመጠቅለል ተግባር ነበር። ይህ ተግባር አገር ግንባታ (nation-building, i.e. one state for each nation መፍጠር) አልነበረም። ዓላማውም ለአንድ ሕዝብ አንድ መንግስት ማቆም ሳይሆን፣ አንድ የራሱ መንግሥት ያለው አገር ሌሎችን በእርሱ የመግዛትና፣ “የማስገበር” ነበር። የጀርመንና የጣልያንን ከኢትዮጵያ ጋር ለማመሳሰል መሞከር፣ አገር ግንባታን እና ኢምፓየር ግንባታን አንድ አድርጎ ማየት ነው። ይኼ ስህተት ነው።

የአውሮፓውያኑም፣ የኛም፣ አንድ ዓይነት ፕሮጀክት ነበር (ሁለቱም nation building ወይም empire building ነበር) ቢባል እንኳን የጥፋቱ፣ መጠን፥ የፈጀው ጊዜ፣ ውጤቱ፣ የጭካኔው ደረጃ፣ በፍፁም የሚወዳደርና አንድ ዓይነት ነው የሚባል አይደለም። የሁለቱ አገሮች የወሰዱትን ጊዜና የምኒልክ ዘመቻዎች የወሰዱትን ጊዜ ብቻ በማየት የዘመኑን ልዩነት ማየት ይቻላል። የጭካኔውን ነገር እራሳቸው የንጉሡ ረዳት ፈረንጆችና የቤተመንግሥቱ ዜናመዋዕል ጸሓፊዎች የመሰከሩት ጉዳይ ነውና ከዚያ በላይ ምስክር አያስፈልገውም። በኢትዮጵያ ከ1889-1900 የተፈጀው ሕዝብ ቁጥር በብዙ ሚሊዮኖች ይገመታል። በአንፃሩ፣ በሁለቱ አገሮች አንድ ላይ ያለቀው ህዝብ ጥቂት ሺህዎች ነበሩ። ተመሳሳይ ነው ብሎ መከራከር፣ የራስን ጥፋት ለማሳነስ መሯሯጥ ነው። ይኼም፣ ያለቀውን ሕዝብ ሕይወት ምንም ትርጉም እንደሌለው መቁጠር ነው። የኢትዮጵያ ደቡባዊ ክፍል ሕዝቦች ሕይወት እነአቶ ኤፍሬም አገር ግንባታ ለሚሉት የኢምፓየር ግንባታ ፕሮጀክት የተከፈለ (ቀላል) ዋጋ እንደሆነም መልሳቸው ያመላክታል። ለመሆኑ፣ ጉዳዩ አገር መገንባት እንኳን ቢሆን፣ አገርና መንግሥት ለሕዝብ (ሕይወት) ቤዛ ይሆናል እንጂ ሕይወት የአገርና የመንግሥት ቤዛ ይሆናል እንዴ? ሕይወት ይከፈላል ቢባል እንኳን፣ አቢሲኒያውያን እየተጋነኑ በኢምፓየሩ ውስጥ እንዲኖሩ ሌሎቹ ብቻ ለጥፋት፣ ለጭፍጨፋና ለነጠቃ መሰጠት አለባቸው? ይሄ ነው “የዜግነት ፖለቲካ” ውርስ? ይኼ ነው ግቡ?

የጀርመንና ጣልያን የአገር ግንባታ ሂደት ውጤቱ፣ በአንድ አገረ-መንግሥት ውስጥ እኩል መብት ያላቸውን እኩል ዜጎችን መፍጠር ነበር። የምኒልክ መስፋፋት ውጤቱ ለደቡባዊው ኢትዮጵያ ህዝቦች እኩል ዜግነት ሳይሆን በባርነት መጋዝ፣ መሸጥና መበዝበዝ፣ በመሬታቸው ላይ ገባርነትና ጭሰኝነት ነበር። ውጤቱ፣ እስከዛሬም ድረስ የዘለቀ በሕዝቦች መካከል ያለ የደረጃ ግንኙነት (relationship of hierarchy) ነው።

ለኤፍሬም ማዴቦ ምኒልክ የፈጠሩትና ለልጆቻቸው ያወረሱት “ትልቅ አገር”፣ እንዲህ ያለ የዜጋና የባሪያ ግንኙነት፣ የነፍጠኛ/ የባላባትና የገባር ግንኙነት፣ የጌታና የጭሰኛ ግንኙነት ያለበት ኢምፓየር ነው።

“የዜግነት ፖለቲካ” ተብዬው አዲሱ ሸፍጥ ለዚህ ነው የደረጃ ግንኙነት ያለውን የባርነት ፖለቲካ ለመመለስ የሚጣጣረው ማለት ነው።

ይሄ ማፈሪያ የሆነ የምግባር መታወር ሁኔታ (moral blindness) ነው።

Shame on our blindness!

Tsegaye R. Ararssa

Tsegaye R. Ararssa

I like to die teaching. ...Living on the edge, exploring the borders... in self-estrangement...on exile... never too grounded physically or epistemically...always coming, always longing to arrive...ever in love with words...trying to find voice in/through them...trying to make sense,...ever trying to see the light, and to comprehend the same, and to find utterance...to enchant. ...and more...for there is always more in/to life...And the EXIT, yes, the Exit. Perhaps relief at last, arrival, ... finally, in and through EXIT...
Spread the news
  • 604
    Shares


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked as *