Main Menu

ታላቅ መሆን የሚቻለው ያለፈውን በማንኳሰስና መጪውን በማጨለም አይደለም !

ታላቅ መሆን የሚቻለው ያለፈውን በማንኳሰስና መጪውን በማጨለም አይደለም!

ይህ ትውልድ ካለፈው ዘመን የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት መትጋት ሲኖርበት፣ በጭፍን ድጋፍና ጥላቻ ውስጥ ሆኖ ወደ ተግባር በማይመነዘር ጭቅጭቅ ጊዜውን ማባከን የለበትም፡፡ ታላቅነትን ማግኘት የሚቻለው ታላቆችን ከሚገባቸው በላይ በማግዘፍ ወይም በማዋረድ ሳይሆን፣ አርዓያ የሚሆን የተሻለ ሥራ ሠርቶ በተጨባጭ በማሳየት ብቻ ነው፡፡

በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ ከሚያሰለቹና ከሚያታክቱ ነገሮች አንደኛው፣ ስላለፈው ዘመን ያለው ጽንፍ የረገጠ አተያይ ነው፡፡ ይህ የተዛባና ኢምክንያታዊ አተያይ በዚህ ዘመን ክንውኖች ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ድጋፍና ታቃውሞ እየተሳከሩ ነጩን ጥቁር፣ ጥቁሩን ደግሞ ነጭ በማለት ውዝግብ መፈልፈል ልማድ ሆኗል፡፡ በዚህ ታሪካዊ ወቅት እንኳን ነገሮችን ከማንነትና ከቡድን ጥቅም ጋር ብቻ በማቆራኘት፣ ተስፋ የተጣለባቸው በርካታ ጉዳዮች ሲደበዝዙ ይስተዋላል፡፡ ያለፉ ዘመናትን ቁርሾዎችና መቋሰሎች ለታሪክ ዶሴዎች ትቶ እንደ አዲስ የጋራ አማካይ ከመፈለግ ይልቅ፣ አሰልቺ ትርክቶች ውስጥ ተዘፍቆ መጠዛጠዝ ተለምዷል፡፡ እያንዳንዱ ትውልድ የራሱን ታሪክ የመጻፍ ብቻ ሳይሆን የመሥራት ግዴታ አለበት፡፡ ይህ ግዴታ የሚመነጨው ደግሞ በመጪው ትውልድ ተጠያቂ ላለመሆን ነው፡፡ በመጪው ትውልድ መጠየቅ ካልተፈለገ ደግሞ ከበፊቱ የተሻለ ሆኖ መገኘት የግድ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ትውልዱ ታሪኩን ለመሥራት ሲነሳ ያለፈውን ዘመን ዞር ብሎ መቃኘት የግድ ይለዋል፡፡ በዚያን ዘመን የነበሩ ድርጊቶችን ሲመረምር አንደኛ ስህተት ላለመድገም ትምህርት ያገኛል፡፡ ሁለተኛ የተሻለ ለመሥራት የሚያግዙ ድክመቶችንና ጥንካሬዎችን ይገነዘባል፡፡ ሦስተኛ ለመጪው ትውልድ ልምድ ያጋራል፡፡ ታላቅ መሆን የሚቻለው እንዲህ የማድረግ ብቃትና ድፍረት ሲኖር ብቻ ነው።

እያንዳንዱ ትውልድ የራሱ ጀግኖች አሉት፡፡ እነዚህ ጀግኖች በአገር አስተዳደር፣ በትምህርት፣ በምጣኔ ሀብት፣ በሕክምና፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በጦር ሜዳ ጀብድና በመሳሰሉት መስኮች ሊገኙ ይችላሉ፡፡ አገሪቱ እንደምትገኝበት ሥርዓትና መንግሥታዊ አስተዳደር ዜጎች በየተሰማሩባቸው የሥራ መስኮች ኃላፊነታቸውን ሲወጡ፣ አንዳቸው ከሌላው በተሻለ በሚኖራቸው ትጋትና ውጤት ይከበራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ስማቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል፡፡ በታሪክም ሁነኛ ሥፍራ ያገኛሉ፡፡ በፖለቲካ አቋም፣ በማንነት፣ በእምነት፣ በፆታ፣ ወይም በተለያዩ ምክንያቶች ጎራ እየፈጠሩ የራስን መካብ፣ የሌሎችን የማዋረድ አዘቅት ውስጥ ሲገባ ሰው የመሆን ትርጉሙ ፋይዳ ቢስ ይሆናል፡፡ በሁሉም ነገር መስማማት የግድ ባይሆንም፣ የጋራ የሆነ አማካይ እየፈጠሩ ባለ ውለታዎችን ማሰብ የታላቅነት መገለጫ ነው፡፡ ‹‹ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ ማንም አይፈልገውም›› እንደሚባለው፣ እርስ በርሱ የማይከባበር ትውልድም ሆነ ማኅበረሰብ ተንቆ ይቀራል፡፡ ታላቅነትን ማሰብም አይቻልም፡፡
.
ሌላው መጠቀስ ያለበት ቁምነገር መቀራረብና መነጋገር ባህል በሆነ ቁጥር የጋራ አማካይ ለመፍጠር የሚያስችሉ በርካታ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በኩርፊያ፣ በጥላቻ፣ በቂም በቀልና በመሳሰሉት ክፉ ደዌዎች የተመረዙ ሳይቀሩ መታከም የሚችሉበት ዕድል እየተፈጠረ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ መልካም አጋጣሚ ደግሞ ማኅበረሰቡ ውስጥ በስፋትና በጥልቀት እየዘለቀ ሲሄድ፣ ከአውዳሚ ድርጊቶች በመታቀብ ወደ ሥልጣኔ መሸጋገር ይቻላል፡፡ ታላቅነትም ቅርብ ይሆናል፡፡ ያለፉትን ዘመናት ድርጊቶች ከመጠን በላይ በመኮነን ወይም በተጋነነ ሙገሳ ሰማይ ጥግ በማድረስ ሳይሆን፣ ለመጪው ትውልድ በሚጠቅም መንገድ ታላቅነትን ማሳየት የግድ ይላል፡፡ ታላቅ መሆን የሚቻለው ያለፈውን በማንኳሰስና መጪውን በማጨለም አይደለምና!

– ሪፓርተር

Spread the news


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked as *