Main Menu

በእብሪት ሳይሆን በትሁት የከተሜ ፖለቲካ ከተሜ መሆን ይቻላል–ከተፈለገ!!

በእብሪት ሳይሆን በትሁት የከተሜ ፖለቲካ ከተሜ መሆን ይቻላል--ከተፈለገ!!! - Tsegaye Ararssa

የሌሎችን ሰብዓዊ ክብር (human dignity) በመቀበል፥ ብዝኅነት ባለው አገር ውስጥ አንተና ቡድንህ ከማንም እንደማትበልጡና ከብዙሃኑ አንዱ ብቻ እንደሆናችሁ በማመን፥ በተዛነፈ የኃይል ሚዛን የተገኙ፣ ያልተገቡ መብቶችንና ጥቅሞችን (privileges) ለመተው በመፍቀድ፥ እኩል ዜግነትን የሚቀበል የትሁት ፖለቲካ በማራመድ ከሌላው ጋር አብረህ ለመኖር እስካልተዘጋጀህ ድረስ፣ ሺህ ጊዜ በ’አዲስ አበቤነ’ትና በአገር ሥም ብትፎክር፣ ያንተን ዘረኛ የበላይነት ጥያቄ ለማስተናገድ የሚችል አስተዳደር ቀርቶ ለመስማትም የሚታገስ ጆሮ አታገኝም።

እውነትም ‘አዲስ አበቤ’ ለመሆን ከፈለግህ፣ ለአካባቢው ኦሮሞ ነዋሪ ያለህን ጭፍን ጥላቻና ንቀት ጣል።

በከተማው ላይ “ከእኔ ድምፅ በቀር መሰማት፣ ከእኔ ቋንቋ በቀር መነገር፣ ከእኔ ባህል በቀር መንፀባረቅ፣ ከእኔ ታሪክ በቀር መዘከር፣ ከእኔ ትውስታና ትዝታ በቀር መታወስ የለበትም፤ በተለይ የኦሮሞ የሆነ ምንም ነገር ዝር አይላትም!” የምትለዋን ፉከራህን አቁም።

እውነትም ‘አዲስ አበቤ’ ለመሆን ከፈለግህ፣ የሕዝቡን ቋንቋ ተማር።

የሕዝቡን ባህል፣ ማንነትና ሰብዓዊ ክብር አክብር።

የሕዝቡን ታሪክ በተገቢው ሁኔታ ዘክር።

እውነትም ‘አዲስ አበቤ’ ለመሆን ከፈለግህ፣ የፖለቲካ፣ የባህልና የኢኮኖሚ የበላይነትህን ባልተገባ መንገድ ለማስቀጠል የምታደርገውን ከንቱ ጥረት አቁም።

ከሌሎች ጋር በእኩልነት መኖርን ተለማመድ።

በሌሎች ላይ የበላይነትህን ለማሳየትና ይሄንንም ለማግነንና ለማጋነን የተተከሉ የታሪክና የባህል ‘ቅርሶችህን’፣ ዛሬም ሕዝብን ከሚያደሙበትና ከሚያቆስሉበት ‘የክብር’ አደባባይ አውርደህ ወይ ወደ ሙዚየም፣ አሊያም ወደራስህ መንደር ውሰዳቸው።

እውነተኛ ‘አዲስ አበቤ’ ለመሆን ከፈለግህ፣ የሌሎችን ወደ ከተማው መፍለስ እንዳልተቃወምከው ሁሉ፣ የኦሮሞውን ወደ ከተማው መምጣት፣ በከተማው ውስጥ ያለውንም ኦሮሞ በሰላም፣ በነፃነትና በእኩልነት የመኖር መብት እንዲሁ አክብር።

አይ፣ “የለም፣ እኩልነት አይስማማኝም፣ የበላይነቴ ካልቀጠለ (የኦሮሞ ባዕድነት በሕግ ካልፀና) በቀር መኖር አልችልም” ካልክ፣ አንተ ‘አዲስ አበቤ’ አይደለህም። ለመሆንም ፍላጎት የለህም። አንተ ሕገ-ወጥ ሰፋሪ፣ ንፉግ ነዋሪ ነህ። አንተ ከተሜም ስልጡንም አይደለህም። አንተ ንፉግ ነህ፣ ፖለቲካህም ስድና መደዴ (vulgar) ነው።

ለእኩልነት፣ ለእኩል ዜግነት፣ እና ለመልካም ጉርብትና የማይሆን የመደዴ ፖለቲካህን ይዘህ፣ ባለቤቱን ባዕድ በማድረግ፣ ‘ብቸኛ ባለቤት ነኝ’ በማለት የምትቀጥል ከሆነ፣ አንተው እራስህ የትናንት ወራሪ-ሰፋሪነትህን ብቻ ሳይሆን በነጣቂ ሰፋሪነት (እና የአካባቢውን ነዋሪ በማጥፋት) ለመቀጠል ያለህን የዛሬ ፍላጎት እያፀናህ፣ እራስህን ከከተማው እየነጠልክ ነውና አያስኬድህም። ውጤቱም ለአንተው ለእራስህ አሉታዊ ነው።

ሰው ከሆንክ፣ ቆም ብለህ አስብ! ስልጡን ከሆንክ፣ ያለህበትን ተረዳ። ከአካባቢህ ተስማማ። በትሁታን ፖለቲካ ወግ ከነዋሪው ጋር ‘ተዛምደህ’ ለመኖር ትጋ! ይሄንን በማድረግ ሰፋሪነትን ሽረህ ነዋሪነትን አፅና!!!

የትሁት ፖለቲካ ይብቀል!
settlers can be natives if they want!

 

Tsegaye R. Ararssa

Tsegaye R. Ararssa

I like to die teaching. ...Living on the edge, exploring the borders... in self-estrangement...on exile... never too grounded physically or epistemically...always coming, always longing to arrive...ever in love with words...trying to find voice in/through them...trying to make sense,...ever trying to see the light, and to comprehend the same, and to find utterance...to enchant. ...and more...for there is always more in/to life...And the EXIT, yes, the Exit. Perhaps relief at last, arrival, ... finally, in and through EXIT...
Spread the news
  • 1K
    Shares


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked as *