Main Menu

ስለ ፊንፊኔ/አዲስ አበባ አንዳንድ ነጥቦች

ፊንፊኔ የኦሮሚያ ከተማ ነች - Tsegaye Ararssa

በፊንፊኔ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ውይይት፣ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ነጥቦች ታሳቢ ቢያደርግ ፍሬያማና ውጤታማ ይሆናል። እነዚህን ታሳቢ ባናደርግ፣ ውይይቱም ፍሬ-ቢስ፣ ፖለቲካውም ውጤት አልባ ሆኖ ይቀጥላል።

  1. መልክዓ-ምድራዊ ተጠየቅም (the geographic logic)፣ የታሪክ ማስረጃውም፣ የአገሪቱ የሕግ ድንጋጌዎችም፣ ፊንፊኔ የኦሮምያ መሆኗን ይመሰክርሉ።

ፊንፊኔ የኦሮሚያ ከተማ ነች። ከዚህም ባሻገር፣ የኦሮሚያ መንግሥት ዋና ከተማ፣ የፌደራል መንግሥቱም መቀመጫ ነች። ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በተለያየ ወቅትና ምክንያት፣ ለተለያየ ዓላማ፣ የፈለሱ ነዋሪዎችን የያዘች፣ የህዝቦች መዲና፣ እና የንግድና የፖለቲካም ማዕከል መሆኗም ይታወቃል። በማንኛውም ከተማዋን በሚመለከት ውይይት ውስጥ፣ ይሄ ታሳቢ ሊሆን ይገባል።

  1. በታሪክም፣ በመልክዓ-ምድራዊ ተጠየቅም፣ ሆነ በሕግ፣ ፊንፊኔ በኦሮሚያ ክልል የምትገኝ የፌደራል መንግሥቱ መቀመጫ ነች እንጂ እራሷን የቻለች ክልል አይደለችም። የፌደራል መንግሥቱ መቀመጫ ነች ሲባል፣ የፌደራል መንግስቱ ተቋማት ጽሕፈት ቤቶች ሥራቸውን በዋናነት የሚያከናውኑባት ከተማ ናት ማለት ነው።

በተደጋጋሚ የምናየው ከተማይቱን እንደ ክልል የመቁጠር ስህተት ሊታረም ይገባዋል። አገሪቱ በሽግግር ጊዜ በቻርተር በተዳደረችበት ዘመን (ከ1983-1987 ዓም፣ ወይም እኤአ ከ1991-1995) እራሷን የቻለች ክልል የነበረች ቢሆንም ሕገመንግሥቱ ከፀናበት ጊዜ ጀምሮ ይሄ ክልልነት አብቅቷል።

አሁንም (በታከለ ኡማ አስተዳደር ሥር እየተሞከረ እንዳለው)፣ ከተማዋን ከኦሮሚያ ለመንጠቅ በማሰብ ብቻ፣ (“ብራስልስን እንደ ሞዴል ወስደን) እራሷን የቻለች ከተማ-ክልል (city-state) እናድርጋት” የሚለው አካሄድ ሊታረም ይገባል።

በመሆኑም፣ ፊንፊኔ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የምትገኝ፣ የኦሮሚያ ከተማ የሆነች፣ የፌደራል መንግሥቱ መቀመጫ ነች። በቃ።

  1. የከተማው አስተዳደር ተጠሪነቱ (በቅድሚያ ለኦሮሚያ መሆን ሲገባው፣ ሕገመንግሥቱ ሲረቀቅ በተፈፀመ ስህተት ምክንያት) ለፌደራል መንግሥት የሆነና እራሱን በቻርተር የሚያስተዳድር የከተማ አስተዳደር (municipality) ነው። ተጠሪነቱ (በስህተት) ለፌደራል መንግስቱ (ብቻ) መሆኑ ግን፣ ከተማዋ ከኦሮሚያ ውጭ የሆነች ራስ-ገዝ ከተማ ነች፣ ወይም የፌደራሉ መንግሥት ይዞታ የሆነች ከተማ ነች ማለት አይደለም።
  2. አንዳንዶች አልፎ አልፎ ለመከራከር እንደሚዳዱት፣ የከተማው አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግሥት በመሆኑ ብቻ ከክልሎች (ማለትም ከኦሮሚያ) ነፃ የሆነች የፌደራል ግዛት (Federal District, or Federal Capital Territory) አያደርጋትም፣ አላደረጋትም። በነገራችን ላይ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ አንድም የአገሪቱ ክፍል በቀጥታ ‘የፌደራል ግዛት’ ተብሎ በሕገመንግሥቱም ሆነ በሌላ ከዛ ወዲህ በወጣ ህግ፣ ወይም በሌላ ህጋዊ አስገዳጅነት ባለው ስምምነት የተሰየመ አካባቢ የለም። ከተማዋ የፌደራል መንግሥት መቀመጫ ስትደረግም እንኳን ይህ የተፈፀመው፣ ጥልቀት ባለው ውይይት፣ ወግ ባለው ድርድርና፣ በውል ሳይሆን እንዲሁ ከቀድሞ ዘመን በተወረሰ ልማዳዊ ተጠየቅ ብቻ ነው። የፌደራል መንግሥቱ ‘መቀመጫ የት ይሁን?’ የሚለው ጥያቄ፣ ዛሬም ቢሆን እንደ አዲስ ተነስቶ ውይይት ቢደረግበትም ለአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ብዙ ፋይዳ ይኖረዋል። በዘረፋ የተያዘ ቋሚ ንብረት ላይ ብዙ መቆየት ባለቤት አያደርግምና፣ ባለቤቱ ጥያቄውን ባነሳ ቁጥር ከመበርገግና ሰላም ከማጣትም ያድናል።
  3. የከተማው ነዋሪዎች ባለሙሉ መብት ዜጎች ናቸው፤ ሆነውም ይቀጥላሉ። እራሳቸውንም፣ በመረጡት ተወካይ የማስተዳደር መብት አላቸው። (ይሄ ማንም የማይነፍጋቸው [እና ማንም የማይቸራቸው] ሕገመንግሥታዊ መብታቸው ነው።) በፌደራል ፓርላማ ውስጥ ባሉት ተወካዮቻቸው በኩልም አገሪቱን ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በጋራ ያስተዳድራሉ።

‘አልተወከልንም’ የሚለው የዘወትር አነጋገር፣ ፍፁም ስህተት ብቻ ሳይሆን፣ ለማምታታት የተፈጠረ የፖለቲካ ግነት (political hyperbole) ነው። እውነቱ ግን፣ የከተማው ነዋሪ፣ በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ፣ በ23 ወይም 24 ድምፅ ተወክሎአል። በከተማው ምክር ቤትም እንዲሁ ሙሉ ውክልና አለው (ያው፣ ተመራጮቹ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያልተመረጡ መሆናቸው፣ እንደሌሎቹ ክልሎች ተወካዮች ሀሉ፣ የተመራጮቹ ትክክለኛ ሕዝባዊ ውክልናቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ቢሆንም!)

በተጨማሪም፣ ነዋሪዎቿ የየብሔራቸውን የወል መብትና ጥቅም ለማስከበር የሚያስችል ውክልና በፌደሬሽን ምክር ቤት ውስጥ ባሉ፣ የሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች ተወካዮች ተወክለዋል። በመሆኑም፣ በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ አማሮች እንደ አማራ፣ ኦሮሞዎች እንደ ኦሮሞ፣ ጉራጌዎች እንደ ጉራጌ፣ ስልጤዎች እንደ ስልጤ፣ ተጋሩ እንደተጋሩ፣ ወዘተ፣ ለቁጥራቸው ተመጣጣኝ በሆነ መንገድ ተወክለው አሉ። እርግጥ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት ምርጫ፣ እስካሁን ሲደረግ እንደቆየው፣ በክልሎች ምክር ቤት ከሚሆን ይልቅ በቀጥታ በሕዝብ ቢሆን ኖሮ፣ ውክልናው የተሻለ ይሆን ነበር። ነገር ግን እስካሁን ባለው አሰራርም ቢሆን ማንም በፌደሬሽን ምክር ቤት ውስጥ ያልተወከለ ብሔር እስከሌለ ድረስ–ሁሉም ብሔር በምክር ቤቱ ውስጥ ተወክሏል ባልን መጠን የከተማይቱ ነዋሪዎችም ተወክለዋልና–‘የከተማዋ ነዋሪዎች አልተወከሉም ብሎ ማለት ብዙ ርቀት የሚያስኬድ ክርክር አይሆንም። ብሔር የሌለው የከተማ ነዋሪ የለምና። ከብዙ ብሔር የተወለደም ሰው እንኳን ቢኖር፣ ባለብዙ ብሔር ሆኖ በብዙ ተወካዮች ይወከል ይሆናል እንጂ፣ ሳይወከል የሚቀርበት ምንም ዓይነት ሁኔታ የለም። (በመሆኑም፣ አንዳንዴ በውሸት ‘ብሔር የለንም’ በማለት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ‘እንደ ብሔር፣ ወይም በወል እንደ ሕዝብ፣ አልተውከልንም’ እያሉ አቅል-የለሽ ጩኸት ማሰማት፣ ተራ የፖለቲካ መደዴነት ነው።)

የከተማው ሕዝብ እንደ ግለሰብ ዜጋም፣ እንደ ህዝብም (በወል) ሙሉ መብት ያለው ሕዝብ ነው። ከተማዋ፣ በእርግጥም የአገሪቱ ሕዝቦች ሁሉ መዲና በመሆኗ እውነተኛ የሕብራዊነት(የብዝሓነት) ተምሳሌት ሆና መኖር ትችላለች፣ ልትሆንም ይገባል። ከዚህ ይልቅ፣ በአንድ ብሔር ማንነት ልክ በተሰራ አፋኝ ኢትዮጵያዊነት ጭምብል ሥር ተደብቆ፣ ‘እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ እንጂ ብሔር የለኝም’ እያሉ መመፃደቅና ‘ያው…ብሔር አለኝ ግን በብሔሬ አትጥሩኝ’ ማለት ተገቢ አይሆንም። (ይሄ የከተማዋ ‘በረራ’ነት አሉባልታም የበረከተው እንደዚህ ዓይነት ወገኖች ብቻ መሆኑም ይሄንን በግልፅ የሚያሳይ ይመስለኛል።)

  1. ፊንፊኔ የኦሮሚያ ከተማ ነች ማለት፣ ኦሮሞ ያልሆነ ሰው በእኩልነት አይኖርባትም ማለት አይደለም። እንዲህ ሊባል አይገባም። ተብሎም አያውቅም። እንዲህ ያለ አስተሳሰብ፣ በሕግም በፖለቲካ ሥነምግባርም ዓይን ሲታይ ነውር የሆነና መቼም ቢሆን፣ በፍፁም ሊስተናገድ የማይገባው አስተሳሰብ ነው። (ታድያ፣ በሌሎች ላይ–በተለይ በከተማው ባለቤት በሆኑ ሕዝቦች ላይ–የበላይ ሆኖ ለመኖርና ያልተገባ መብት [privilege] መጠየቅም እንደዚሁ ነውር ነውና፣ ይሄም አብሮት ሊወገዝ ይገባዋል።)

ይሄ የከተማዋን የኦሮሚያ መሆን ተቀብሎ እንደ ባለ ሙሉ መብት ዜጋ፣ በእኩልነት ተከብሮ መኖር ማለት፣ በተጨባጭ ሲታይ ምን ማለት ነው ቢባል፣ የከተማው አስተዳደር ተጠሪነቱ ለኦሮሚያም ይሆናል ማለት ነው እንጂ፣ ነዋሪው ሁሉ በግድ ኦሮምኛ ተናጋሪ ይደረጋል ማለት አይደለም። ነገር ግን፣ ለምሳሌ የከተማው መስተዳድር የሥራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ ቢሆን ለአሰራር ቅልጥፍና ጠቃሚነት አለው፣ ለኦሮሞ ነዋሪዎችና ለክልሉም ተገቢውን አክብሮት መስጠትን ያሳያል። እንደእውነቱ ከሆነ ይሄን ማድረግ፣ ከከተማው ህሕብራዊነት አንፃር፣ ሌሎች ቋንቋዎችንም የስራ ቋንቋ ለማድረግ መንገድን አመላካች ነው። በኔ ምርጫ ቢሆን፣ ፊንፊኔ፣ የሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች መናኸሪያ በመሆኗ የከተማው መስተዳድር የሥራ ቋንቋ፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ቢሆኑ ይሻላል እላለሁ። አዲሱና እውነተኛው ሁሉን አቃፊ ኢትዮጵያዊነትም በዚህ ሕብራዊ ቀመር ላይ ይመሠረታልና። በዛ ላይ፣ እራሱን እንግዳ ተቀባይ ብሎ ከሚያንቆለጳጵስና ለውጭ አገር ቋንቋዎች እንኳን መስሪያ ቤቶቹን፣ ሕጎቹን፣ የልጆቹን ትምህርት ቤቶች እና የግል ጓዳውን ጭምር (በቴሌቪዥን ለሚተላለፉ የውጭ ፕሮግራሞች) ክፍት አድርጎ ለሚኖር ማሕበረሰብ፣ ‘የራሱ የሆኑ’ ሕዝቦችን ቋንቋዎች በሥራ ቋንቋነት አለመቀበል ግብዝነት ይሆንበታል

እነዚህን ነጥቦች ታሳቢ አድርገን ብንወያይ ወደፊት ልንራመድ የምንችል ይመስለኛል። ካልሆነ ግን…

 

Tsegaye R. Ararssa

Tsegaye R. Ararssa

I like to die teaching. ...Living on the edge, exploring the borders... in self-estrangement...on exile... never too grounded physically or epistemically...always coming, always longing to arrive...ever in love with words...trying to find voice in/through them...trying to make sense,...ever trying to see the light, and to comprehend the same, and to find utterance...to enchant. ...and more...for there is always more in/to life...And the EXIT, yes, the Exit. Perhaps relief at last, arrival, ... finally, in and through EXIT...
Spread the news
  • 1.6K
    Shares


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked as *