Main Menu

አሀዳዊ ስርአትን ለማስፈን በሚደረግ ከንቱ ሙከራ ሀገር ሊፈርስ ይችላል

Rediet Tamire

ኦዴፓ ጥልቅ መታደስ አድርጌያለሁ ብሎ “ኢትዮጵያ ውስጥ የመደብ እንጂ የብሄር ጭቆና አልነበረም” ብሎ የእውነት መቃብር ላይ ቆሞ ቂጥ መላስ ሲጀምር የቁልቁለቱ መንገድ ተጀመረ። የብሄር ጭቆና ነበር ማለት ጨቋኝ ብሄር ነበር ማለት አይደለም። ጨቋኞች ምን ግዜም ገዢ መደቦች ናቸው። ጭቆናው ግን የብሄርም የመደብም dimension ሊኖረው ይችላል። ደግሞም ነበረው። ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ሀብት መሬት ነው የመሬት ስሪት (land tenure) እና መብቶች (land rights) ደግሞ በሰሜኑና በደቡቡ የሀገሪቱ ክፍል አንድ አይነት አልነበሩም። ኦዴፓ ይሄ ይጠፋዋል ማለት ይከብዳል። ነገር ግን ማስደሰት የፈለገው አካል ስለነበረ መርህ አልባ መልመጥመጥ በማረግ ስህተቱን አንድ ብሎ ጀመረ።

ፍቅርን የተራበው ኦዴፓ የአንድ ሁለት ቀን ጭብጨባን ለመሸመት ብሎ ያልደፈጠጠው መርህ የለም ለማለት ይቻላል። ነገም ምን ያደርጋል አይባልም። ኦዴፓ abusive relationship ውስጥ ሆና እንጥፍጣፊ ድጋፍ (approval) ለማግኘነት የማትፈነቅለው ድንጋይ እንደሌ ፍቅረኛ ይመሰላል። ወከባው ጠንከር ካለበት ኦዴፓ ነገ ተነስቶ አሀዳዊት ኢትዮጵያ ወይንም ሞት የሚል መግለጫ ቢያወጣ አይደንቀኝም። ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በቅርቡ እኔ ብሄር ምን እንደሆነ በማይታወቅበት አምቦ ውስጥ ነው ያደኩት ብሎ ሲወተውት እኔንም በልቤ እጄን ምታ እስቲ ታኬ አስብሎኛል። መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ግን ይሄ ነው። ይሄን ያህል ቂጥ መላስ እና መወትወት ለምን አስፈለገ? በማባበል የሚፈጠር መርህ አልባ ወዳጅነት መናናቅን ከማምጣት ውጩ ዘለቄታ አይኖረውም። በመርሀቹ ላይ ጸንታቹ ቁሙ፣ የህዝባችሁን ፍላጎት በኩራት እና በትክክል represent አድርጉ። ኦሮሞውን፣ ሲዳማውን፣ ሶማሌውን፣ ትግሬውን፣ አፋሩን እና ሌሎችም በፌደራሊዝም የማይደራደሩ ህዝቦችን ማዳመጥ ካልፈለጋቹ ማንን ነው የምታዳምጡት? ማንን ነው የፈራችሁት? ግልጽ ንገሩን። ህግን ማስከበር አለመቻላችሁን በህብረብሄራዊ ፌደራሊዝም ላይ ለማላከክ መሞከር በእውነት አሳፋሪ ተግባር ነው። ህብረ ብሄራዊ ፌደራሊዝም ገና ተጠናክሮ ይቀጥላል። ደቡብ ላይም በህገ መንግስቱ መሰረት ይተገበራል። የፌደራል መንግስት የስራ ቋንቋዎች ገና 4-5 መሆን አለባቸው። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ሌሎች ቋንቋዎችን የሰፈር ቋንቋ በማድረግ ቀስ በቀስ (gradually) እንዲጠፉ እና የአንድ ቋንቋ እና ባህል hegemony እንዲሰፍን ለማድረግ የሚደረግ ሙከራ በፍጹም አይሳካም።

ኦዴፓ እና መሪው ጠቅላይሚኒስር አብይ አህመድ የሚናገሩት ነገር consistency ስለሌለው ትክክለኛው አቋማቸው ምን እንደሆነ ለማወቅ እንኳን አዳጋች ሆኖአል። መንግስት የህግ የበላይነትን ማስከበር ካለመቻሉ ጋር ተዳምሮ የሚስተዋለው መርህ አልባነት እና የአቋም መዋዠቅ ጸረ ፌደራሊስት ሀይሎችን ድፍረት ሰጥቶ አሁን ለምናየው አላስፈላጊ መፋጠጥ ዳርጎናል። ህግን ማስከበር ያቃተው መንግስትም ይሁን ቀኝ ዘመም ሀይሎች አገሪቱ ላይ ለተፈጠረው ችግር በዋነኝነት ተጠያቂው የብሄር ፖለቲካ ነው በሚል የብሄር ፌደራሊዝሙን scapegoat ለማድረግ ያኮበከቡ ይመስላሉ። አንድ ስሙን ጠቅሼ ማስተዋወቅ በማልፈልገው ፕሮግራም ላይ በቀረበ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሚደረግ ውይይት ላይ አንድ የውይይቱ ተሳታፊ የሰጠው ሀሳብ ቀልቤን የያዘ ነበር። ሰውዬው ሀሳቡን ሲሰጥ “አሁን እየተፈጠረ ያለውን ነገር በአንድ መልኩ ጥሩ ነው። ሰው የብሄር ፌደራሊዝምን ፈጽሞ እንዲጠላ ያደርጋል። ከዚ በኋላ ከፈለግን የኢምፔርያል (imperial) ስርአትን ሁሉ መመለስ እንችላለን” በማለት ነበር የተናገረው። በእርግጥ የኢምፔርያል (imperial) ስርአት ይመለሳል የሚል ቅንጣት ታህል ስጋት የለኝም ነገር ግን አሀዳዊ ስርአትን ለማስፈን በሚደረግ ከንቱ ሙከራ ሀገር ሊፈርስ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ።

መንግስት ሆይ ህግ ካልተከበረ የሰፈር ጉልበተኛም እኮ ሰፈሬ አትድረሱ ማለቱ አይቀርም። ሰው የሚሞትባቸው በሰፈር እና ሰፈር መካከል የሚደረጉ የ ግሩፕ (group) ጸቦች የአዲስ አበባ የቅርብ ግዜ ትዝታዎች ናቸው። ሰፈርተኝነት ሁሌም ይኖራል። ጥያቄው ያ ወደ ጸብ እንዳያመራ ካመራም እንዳይደገም የሚያደርግ የህግ የበላይነት አለ ወይ ነው። እኛ ልጆች እያለን አዲስ አበባ ውስጥ በሰፈር ተደራጅተው፣ ሰፈሩ የግል ርስታችን ነው የሚሉ፣ ሰው ማንኛውንም እቃ በመኪና አስጭኖ ሲያመጣ የራስህን እቃ ማውረድ አትችልም፣ እኛ በተመንነው ዋጋ እኛው እናወርደዋለን የሚሉ የሰፈር ጉልቤዎች ሰውን እንዴት መከራውን ያበሉት እንደነበር ቢያንስ በኔ እድሜ እና ከዛ በላይ ያለን እናውቀዋለን። ድንገት ከሰፈርህ ውጪ አራድነት ተጠናውቶህ ኬፕህን ወደኋላ አዙረህ በቄንጠኛ አረማመድ እንደመደነስ እያልክ (“እያነጀብክ”) ከሰፈርህ ውጪ ስትሄድ ከተረገመችው የስልክ እንጨት ስር ሰብሰብ ብለው ከማይጠፉት “ባለሰፈሮች” አይን ውስጥ ከገባህ ተጠርተህ “ከቦ የመምከር አገልግሎት” ሁሉ ይሰጥህ ነበር። ሰው ሰፈር ብትገኝ አንተን አይርገኝ በሚባልበት በዛ ግዜ የየሰፈሩ የጦር ፊት አውራሪዎች ሁሉ ነበሩ። ከትልቅ እስከ ትንሹ ከሚያሸብሩት ውስጥ በቅጽል ስማቸው ገጀራው (በገጀራ ምን ጀብድ ፈጽሞ ያ ስም እንደተሰጠው መገመት ትችላላቹ)፣ቺቺ፣ አሸብር (ይሄኛው በሞተር የታገዘ ሽብር ነበር የሚፈጽመው። Body builder ነገርም ነበር) ወዘተ ጥቂቶቹ ናቸው። አሁን እኔ በቀልድ መልክ ሳወራው ቀላል ይመስላል እውነታው ግን እኛ ልጆች እያለን ይሄ ሰፌሬ እና ሰፈርህ በሚባል የሚፈጸም ስርአት አልበኝነት ትልቅ የደህንነት ስጋት ነበር። አሁን ላይ ግን የተደራጀ የሰፈር ጠብ አዲስ አበባ ላይ በጣም አልፎ አልፎ ካልሆነ አይሰማም። የስልክ እንጨቱም እፎይ ያለ ይመስለኛል። እንዴት ተቀረፈ? ቁርጠኝነት የተሞላበትን ህግን የማስከበር እርምጃ በመውሰድ። አሁንም እላለሁ የህግ የበላይነት ባለበት ሀገር ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሊፈናቀሉ፣ ሊሰደዱ አይችሉም። ከላይ እስከታች ተጠያቂነትን ማስፈን ካልተቻለ፣ የህግ የበላይነትን ማስፈን ካልተቻለ፣ ለፖለቲካ ትርፍ እውነታን ማድበስበስ እና በሰው ህይወት መቆመር እስካልቆመ ድረስ የማንወጣው አዘቅት ውስጥ መግባታችን አይቀሬ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የብሄር ፌደራሊዝም ከ 27 አመት በላይ ሆኖታል እንደዚ በየከፍተኛ ደረጃ (large scale) መፈናቀል እና ግጭት ግን አሁን የተጀመረ ነው። ይህ በእውነቱ የሚያመላክተው ችግሩ የፌደራሊዝሙ ሳይሆን የመንግስት የህግን የበላይነት ማረጋገጥ አለመቻል መሆኑን ነው። የብሄር ፌደራሊዝሙ ተጠናክሮ ይቀጥላል። አሁን እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች ሀላፊነት ላለመውሰድ የብሄር ፌደራሊዝምን እንደ scapegoat መጠቀም ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል። መልመጥመጡን እና ቂጥ መላሱን ትታቹ ህግን አስከብሩ። እኛ ገና እስከ አሁን ደቡብ ላይ በሚገባ ያልተተገበረው ፌደራሊዝም በሚገባ ተተግብሮ ህብረብሄራዊት ኢትዮጵያ ተጠናክራ ትቀጥላለች የሚል እምነት አለን!

Dr. Rediet Tamire

Dr. Rediet Tamire

Dr. Rediet Tamire studied PhD in Molecular Genetics at University of New Hampshire. He is currently working at the university of Maryland school of medicine as a researcher.
Spread the news
  • 510
    Shares


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked as *